በአርባምንጭ ከተማ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር ታላቅ ሩጫ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የጎዳና ላይ ሩጫው በህዝብ ተሳትፎና በክልሉ መንግሥት ድጋፍ እየተገነባ ለሚገኘው የአርባ ምንጭ ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ እንዲሁም በከተማው የሚከበረውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
በሩጫው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የክልልና የዞን የሥራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂው አትሌት ሙክታር ኢድሪስና ታዋቂ ግለሰቦች፣ የ12ቱም ዞኖች ተወካዮች እንዲሁም ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
መነሻውንና መድረሻውን ጋሞ አደባባይ ባደረገው የጎዳና ላይ ሩጫ በወንዶች አትሌት መክሊት መኮንን አሸናፊ ሲሆን÷ ሙሉቀን ታደለ 2ኛ፣ ሳሙዔል አብርሃም 3ኛ በመሆን ሩጫውን አጠናቀው የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል።
በሴቶች ህሊና ሚልኪያስ አንደኛ በመውጣት ስታሸንፍ በፀሎት አረጋ 2ኛ፣ ሀገር ምንአለ 3ኛበመውጣት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል።
ታላቁ የጎዳና ላይ ሩጫ አንድነትንና አብሮነትን የሚያጎላ እንደነበርም መገለጹን የጋሞ ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ከጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሩ በተጨማሪ የተለያዩ የሰርከስ ትርዒቶችና ስፖርታዊ ትዕይንቶችና አዝናኝ ኩነቶች ለታዳሚው ቀርቧል።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአርባምንጭ ከተማ ከነገ ጀምሮ እስከ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል፡፡