Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ፓኪስታን በአቪዬሽን ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) እና የፓኪስታን የአቪዬሽን ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ አህሳን አሊ ማንጊ በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸውን ትብብር በማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

በሀገራቱ መካከል የአቪዬሽን ትስስርን ለማሳደግ እንዲሁም የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር በሚያስችሉ የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካራቺ በጀመረው በረራ ፓኪስታንን ከኢትዮጵያ ባለፈ ከአፍሪካ ጋር ለማስተሣሠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡

ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሌሎች የፓኪስታን ከተሞች በረራ መጀመሩ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በፓኪስታን እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የመንግሥት ለመንግሥት፣ የሕዝብ ለሕዝብ እና የንግድ ለንግድ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ያለመ የፓኪስታን “ሉክ ኤንድ ኢንጌጅ አፍሪካ” ፖሊሲዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተጫወተ ያለውን ወሳኝ ሚናም አብራርተዋል።

በዓለም ላይ ካሉ አንጋፋ ግንባር ቀደም አየር መንገዶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው አገልግሎት በፓኪስታን ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነቱ እያደገ መምጣቱንም ነው አምባሳደሩ ያስረዱት፡፡

አህሳን አሊ ማንጊ በበኩላቸው አፍሪካን ወደ ፓኪስታን በማቅረብ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተጫወተ ያለውን ወሳኝ ሚና አድንቀዋል፡፡

በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማሳደግም የፓኪስታን መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.