ቻይና ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ የምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት ብትሰራ የጋራ ጥቅም ያስገኛል – አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ የምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት ብትሰራ ለሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
አቶ መላኩ አለበል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ቸን ሄይ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ቻይና በኢትዮጵያ ካላት ጉልህ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በተጨማሪ ከኢንዱስትሪ የምርምርና ጥናት ተቋማት ጋር ብትሰራ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በቅንጅት መስራቱ ለሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በውይይቱ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ለመስራት፣ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮችን ችግር ለመፍታትና በኢትዮጵያ የሚቋቋመውን የአፍሪካ ኢንዱስትሪ የልህቀት ማዕከል ወደ ስራ ማስገባትን በተመለከተ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡