Fana: At a Speed of Life!

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያንጸባርቅና አንድነትን የሚገነባ መሆን አለበት – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያንጸባርቅ፣ ዲፕሎማሲን የሚያሳልጥ እና አንድነትን የሚገነባ መሆን አለበት ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማብሰሪያ እና ስራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በግራንድ ኤሊያና ሆቴል እየተካሄደ ነው።

በመርሐ-ግብሩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የሚዲያው አመራሮች የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ተባባሪ አዘጋጆች፣ የሚዲያው አጋሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በመርሐ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፥ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት መዋሃድ በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

ሁለቱ ተቋማት ህብረ-ብሔራዊነትን ለመገንባት ቁርጠኝነታቸውን ማሳየታቸውን አስታውሰው ፤ አዲሱ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዜጎች ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር ረገድ የላቀ ስራ እንደሚሰራ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ብልሹ አሰራርን በማጋለጥ የአገልግሎት አሰጣጥን ያሻሽላሉ ፤ የሀሰተኛ እና የጥላቻ መረጃን ይመክታሉ ፤ በሙሉ የጋዜጠኝነት ስብዕና፣ በጥራትና በፍጥነት ይሰራሉ ብለዋል።

ሚዲያው የመንግስትን አቅጣጫ በትክክል ለሕብረተሰብ ለማድረስ በስፋት መስራት እንዳለበት ገልጸው፤ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚያገለግል ተአማኒና አስተማማኝ ወቅታዊ መረጃዎችን ለዜግች ተደራሽ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዚህም የመንግስት ኮሙኒኬሽን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ ሚዲያው ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያንጸባርቅ፣ ዲፕሎማሲን የሚያሳልጥ እና አንድነትን የሚገነባ መሆን አለበት ብለዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.