ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገዢ ትርክትን በማስረጽ ረገድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገዢ ትርክትን በህብረተሰቡ ዘንድ በማስረጽ ረገድ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አሳሰቡ።
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማብሰሪያ እና ስራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በግራንድ ኤሊያና ሆቴል እየተካሄደ ነው።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የሚዲያው አመራሮች የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ተባባሪ አዘጋጆች፣ የሚዲያው አጋሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ አቶ አደም ፋራህ ባስተላለፉት መልዕክት ፥ አዲስ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ተቋም በመፈጠሩ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚዲያ የነጻነት መርህን መሰረት በማድረግ እንዲዋቀር መሰራቱን መዋቀሩን ገልጸዋል።
የሚዲያ ተቋማት ብዛት እና ተደራሽነት ላይ በትኩረት መሰራቱን የገለጹት አቶ አደም ፋራህ ፥ ፋና እና ዋልታ የመንግስት ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ላይ በስፋት መስራታቸውን አስታውሰዋል።
ውህደቱ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪ፣ ሚዛናዊና የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀ ሚዲያ ፈጥሯል ብለዋል።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገዢ ትርክትን በህብረተሰቡ ዘንድ በማስረጽ ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበው ፥ ብሔራዊና ገዢ ትርክትን በማስረጽ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጎላና የሚያስተዋውቅ ተጽዕኖም እንዲፈጥር ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።
ሚዲያን በተገባ መንገድ ከተጠቀምን ሀገርን የምንገነባበት ባልተገባ መንገድ ከተጠቀምነው ደግሞ ሀገር እስከማፍረስ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በመላኩ ገድፍ እና አመለወርቅ ደምሰው