Fana: At a Speed of Life!

በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማምጣት እየሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማምጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫ፤ በህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ ላይ የወደቁና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ በዋናነት በጃፓን ቶኪዮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከማይናማር መንግስትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር እየመከረ ነው ብለዋል፡፡

በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎችንም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ስራ የተጀመረ መሆኑን ገልፀው፥ ወደ ሀገራቸው መመለስ ከሚፈልጉ 2 ሺህ ኢትዮጵያውያን መካከል የመጀመሪያዎቹ በሚቀጥለው ሣምንት ወደ ኢትዮጵያ ችንደሚመጡ ተናግረዋል።

ይህ ውጤት በዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ስራዎች እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ ትከረት ተደርገው ስለተሰሩ ስራዎች ያብራሩት ቃል አቀባዩ፤ የ24 ሀገራት አምባሳደሮች ለፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ሁለት ኤምባሲያቸውን በአዲስ አበባ ለመክፈት ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙ ሀገራት ይገኙበታል ተብሏል።

እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር) ከተለያዩ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቁና በሚያስከብሩ ሁኔታዎች ላይ ተመስርተው ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም በታህሳስ ወር የበርካታ ሀገራት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ያሉት አምባሳደር ነቢያት፥ ይህም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጨማሪ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማካሄድም በርካታ ስራዎች እየተሰሩና እየተገመገሙ ይገኛሉም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የወሰደችው ሁሉ አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤት እንዲገኝ እያረገ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በዓለምሰገድ አሳዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.