በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ትግበራ በተገኙ ስኬቶችና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ የምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ የሰው ሃብት ልማት ቀጣናዊ ዳይሬክተር ትሪና ሃቄ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፥ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አኳያ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
በዚህም በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አያይዘውም ፥ በሀገርአቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል፡፡
በዓለም ባንክ የምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ የሰው ሃብት ልማት ቀጠናዊ ዳይሬክተር ትሪና ሃቄ በበኩላቸው ፥ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ትልቅ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የማህበረሰብን ኑሮ ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙ እንቅስቃሴዎች ውጤት ማሳየታቸውን ነው ገለጹት፡፡
በገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በቀጣይ የትግበራ ምዕራፉ አዳዲስ እሳቤዎችን እና የትኩረት አቅጣጫዎችን በማካተት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው መገለጀጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡