የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅን ጨምሮ ሶስት አዋጆች ፀደቁ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ4ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅን ጨምሮ ሶስት አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል።
የኢትዮጵያ ሕንፃዎች አዋጅ በነባሩ ሕግ በአፈፃፀም የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ፣ የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽነት የሚያረጋግጥ፣ የግንባታ ጥራትና የሀብት ብክነት ችግሮች የሚቀርፍ፣ ግልፅና ለአተገባበር ምቹ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል መሆኑ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ የኢትዮጵያ ሕንፃዎች አዋጅን በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡
በተመሳሳይም የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ ሪፖርትና የውሳኔ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
የሪል ስቴት ልማቱ አቅርቦት እጅግ ወደኋላ የቀረና የህዝቡን ፍላጎት የማያሟላ በመሆኑ የማይንቀሳቀስ ንብረት ግመታ ስርዓቱ ዘመናዊና በመረጃ የተደገፈ ተገማች ዋጋ እንዲኖረው ማድረግ በማስፈለጉ እና በማይንቀሳቀስ ንብረት ገበያው ግልጽነት መጓደሉ የኢኮኖሚ መዛባት እያስከተለና የመንግስትን ጥቅም የሚያሳጣ እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስችል አዋጅ መሆኑን ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አዋጁን በሁለት ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
በመቀጠልም ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ አዋጅን ለማፅደቅ የቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ማዳመጡን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ምክር ቤቱ ረቂቁን ከመረመረ በኋላ አስፈላጊነቱን በሙሉ ድምፅ የተቀበለው በመሆኑ በቀረበው ረቂቅ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ የኤሌክትሮኒክስ ፊርማ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል፡፡