ግለሰብን በመጥለፍ የ10 ሚሊየን ብር ቼክ ወስደዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግለሰብን አስፈራርተው በመጥለፍ የ10 ሚሊየን ብር ቼክ ወስደዋል ተብለው የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ችሎት ነው።
ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች 1ኛ ኤሳቱ ፍቃዱ ኡርጌ ፣ 2ኛ ም/ሳ ተማም አብዱልቃድር፣ 3ኛ ምትኩ ቦቦ ወልተጂ፣ 4ኛ ዳዊት መላኩ አያና እና 5ኛ ዳግም መላኩ አያና ናቸው፡፡
የፍትህ የሚኒስቴር የልዩ ልዩ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ 1ኛ ክስ፡- በሁሉም ተከሳሾች በ1996 ዓ/ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ/፣አንቀጽ 586፣ አንቀጽ 590 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡
በዚህም ክስ ላይ እንዳመላከተው ተከሳሾች አንድ ለጊዜው ያልተያዘ ግብረ-አበራቸው ጋር በመሆን የማይገባቸውን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰዉ ለማስገኘት በማሰብ በጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ሲሆን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታዉ እናት ት/ቤት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ 1ኛ ተከሳሽ ከግል ተበዳይ ከሆነው ግለሰብ ጋር ቀድሞ የነበራቸው የንግድ ግንኙነት እቃ አመጣልሃለሁ በማለት ቃል የገባቸውን ፀረ-አረም ኬሚካል ባለማስመጣቷ ምክንያት ቀድሞ የግል ተበዳይ የከፈላት ገንዘብ ስለነበረ ገንዘቡን ዳሽን ባንክ አካባቢ መጥቶ እንዲወስድ ነግራው እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል።
በዚህ መልኩ የግል ተበዳይም 1ኛ ተከሳሽ ወዳለችው ስፍራው ሲደርስ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እና ያልተያዘው አንድ ግብረአበራቸው ጋር በመሆን ኮድ 2- አ/አ የሆነ ዶልፊን መኪና በመውረድ ወደ ግልተበዳይ ተጠግተው ማንነቱን ካረጋገጡ በኋላ “እኛ የህግ ሰዎች ነን… በህግ ትፈለጋለህ መኪና ውስጥ ግባ ” በማለት የመጡበት መኪና ውስጥ አስገድደው ማስገባታቸው በክሱ ተጠቅሷል።
ከዚህም በኋላ ተከሳሾቹ የሰው እንቅስቃሴ ወደማይበዛበት ቅያስ ስውር ቦታ በመውሰድ 1ኛ ተከሳሽ በስልክ ደውለው ወዳሉበት ቦታ እንድትመጣ ካደረጉ በኋላ 3ኛ ተከሳሽ የግል ተበዳይን ስልክ አስገድዶ በመቀማት ከግል ተበዳይ ንግድ ባንክ ሂሳብ ወደ በ1ኛ ተከሳሽ ሂሳብ 519 ሺህ ብር በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት እንዲተላለፍ ማድረጋቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ተገልጿል።
ከዚህ በኋላ ደግሞ የ10 ሚሊያን ብር የገንዘብ መጠን ያለውን ቼክ በማስገደድ ከወሰዱ በኋላ ህግ ቦታ የምትሄድ ከሆነ ቤትህንና ሚስትህን አይተናል እንገልሃለን ብለው በማስፈራራት ከመኪናው ላይ እንዲወርድ አድርገው የተሰወሩ መሆኑ ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ሰውን በመጥለፍ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በሁለተኛ ክስ ደግሞ በ3ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበ ሲሆን ፥ ይኸውም ተከሳሽ በጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም በጉ/ክ/ከ//08 ክልል ልዩ ቦታው እምቢልታ ሆቴል አካባቢ ተከሳሽ በውክልና የሚያስተዳድረውን ዶልፊን መኪና እያሽክከረ ሲሄድ በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ተሽከርካሪው ፍተሻ ሲደረግበት ፍቃድ ሳይኖረው ወይም የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሳይኖረው 1ኛ ቫይታሚን B-12 የአጥንት ማጠንከሪያ 8 ፓኬት በውስጡ 10 ካርቶን የያዘ፣ 2ኛ ክሎሪን የወባ በሽታ መከላከያ ብዛቱ 24 ፓኬት 3ኛ አንድ ካርቶን የማደንዘዣ መድኃኒት፣ 4ኛ የስኳር በሽታ መለኪያ 124 እሽግ 5ኛ የስንፈተ ወሲብ መከላከያ 15 ግራም 03 መድኃኒቶችን በመኪናው ውስጥ የተገኘ መሆኑ በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሶ ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት ወደሀገር ውስጥ ለማስገባት ወይም ለማካማቸት ወይም ለመያዝ ወይም ለማጓጓዝ ወይም ለመሽጥ ወይም ጥቅም ላይ ለማዋል፣ ለማዘዋወር የሚያስችል ፍቃድ ሳይኖረው ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት ወይም መድኃኒት ይዞ በመገኘት ወንጀል ተከሷል፡፡
በ3ኛ እና በ4ኛ ክስ ላይ ደግሞ በ1ኛ እንዲሁም በ3 ኛ ተከሳሾች ላይ በተደራቢነት በቀረበ ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ በተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በባንክ ሂሳባቸው ማዘዋወር በሚል ተጠቅሶ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በአጠቃላይ በዚህ መልኩ በተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ ያቀረበው ክስ ዝርዝር በችሎት የደረሳቸው ሲሆን ፥ ተከሳሾቹ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት ጠይቀው ከዐቃቤ ህግ ጋር ክርክር ተደርጓል፡፡
ፍርድ ቤቱም መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሕዳር 30 ቀን 2017 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ