ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር) ከትግራይ ክልል የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከትግራይ ክልል የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የፌዴራል መንግስትና የትግራይ ክልል አመራሮች በክልሉ የጸጥታና የፖለቲካ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ፥ በክልሉ የሚታዩ ችግሮችን እንዴት በጋራ መፍታት እንደሚገባ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በተለዩ አንኳር ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ የጋራ አቅጣጫዎች መሠረት በጋራ ለመስራትና የክልሉ ህዝብ የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ፍላጎት ለማሟላት አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር መግባባት ላይ መደረሱም ነው የተገለጸው፡፡
በተለይም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው የሚመለሱበትን ሁኔታና ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ህይወት የመመለስ ሂደት በትኩረት የሚሰራበት እና የሚሳለጥበት ሁኔታ ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች አጠቃቀም ህጋዊ በሆነ አግባብ የህዝብንና የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንዲሆን፣ ለህዝብ የሚቀርቡ የመንግስት አገልግሎቶች የሚሻሻሉበትና የህዝብን ፍላጎት የሚመጥኑ እንዲሆኑ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ስራ እንዲሰራ ተገቢው አቅጣጫ በውይይቱ መለየቱም ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም ጊዚያዊ አስተዳደሩ ክልላዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ያለበትን ሃላፊነት ለመወጣት በሚያስችለው አግባብ ላይም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡