የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መመስረት ትልቅ ሚዲያ የመገንባት ራዕይን ያሳካል- ርዕሰ-መስተዳድሮች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መመስረት በኢትዮጵያ ትልቅ ሚዲያ የመገንባት ራዕይን ያሳካል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ርእሰ-መስተዳድሮች ገለጹ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) ÷ ኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የሁሉንም ማንነት፣ ባህልና እሴት በማጉላት ወንድማማችነትን ማጠናከር ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንጠብቃለን ብለዋል።
የቀድሞ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና አዲስ ዋልታ የህዝቦችን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ አሰራሮችንና ፖሊሲዎችን ወደ ህዘብ እያደረሱ በህዝብና መንግስት መካከል ድልድይ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
በክልሉ የነበራቸውን አስተዋፅኦም በአዲሱ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዲጠናክር ጠይቀዋል፡፡
በደቡም ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል በይበልጥ ተደራሽነትን ለማሳደግ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ያስፈልገናል ያሉት ርዐሰ መስተዳድሩ ÷ ለዚህም ክልሉ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ÷ በሁለቱ ታላላቅ ሚዲያዎች ውህደት መደሰታቸውን ተናግረው ፤ በውህደቱ የተፈጠረው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚዲያ ተልዕኮን በብቃት እንዲሚያረጋግጥ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ አንጋፋ ሚዲያዎች መጣመር በዚህ ረገድ ሲሰሩ የቆዩትን ስራ ይበልጥ እንዲያድግ አቅም ይፈጥራልም ብለዋል።
እንደሀገር የተፈጠረውን የማህበራዊ ሚዲያ እድገት እና ነፃነትን ተከትሎ ሀሰተኛ መረጃዎች ፈተና መሆናቸውን አንስተው ፤ ሚዲያዎች የሀገርና የህዝቡን ሀቅ ለአድማጭ ተመልካች በማድረስ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ገፅታ ለዓለም ማስተዋወቅ እና ሃቋን ማንፀባረቅ የፋናሚዲያ ኮርፖሬሽን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሚዲያዎችም ድርሻ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የስርጭት ቋንቋዎችን በመጨመር የኢትዮያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በማርታ ጌታቸው