የአፍሪካ ህብረት የትራንስፖርትና ኢነርጂ ቴክኒካል ኮሚቴ የተለያዩ ረቂቅ ስትራቴጂዎችን አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት የትራንስፖርትና ኢነርጂ ቴክኒካል ኮሚቴ የአህጉሪቱን ትራንስፖርትና ኢነርጂ ለማሻሻል የተዘጋጁ የተለያዩ ረቂቅ ስትራቴጂዎችን አጽድቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የትራንስፖርትና ኢነርጂ ቴክኒካል ኮሚቴ ሶስተኛው ልዩ የሚኒስትሮች ስብሰባውን በበይነ መረብ አካሂዷል።
ውይይቱን በሰብሳቢነት የመሩት የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የወደፊቱን የትራንስፖርትና ኢነርጂ ዘርፍ ስትራቴጂ በመቅረጽ ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ የማድረግ የጋራ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
የትራንስፖርት እና የኃይል ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለንግድ መሳለጥ እና ለኢንዱስትሪዎች እድገት ወሳኝ መሆናቸውን አንስተዋል።
ቅንጅትና ትብብርን በማጎልበት፣ የአንድነት መርህን በመከተልና ወንድማማችነትን በማጠናከር የበለፀገች አፍሪካን እውን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የቴክኒክ ኮሚቴው በስብሰባው በትራንስፖርት የዘላቂ አቪዬሽን ኃይል ምንጭ ስትራቴጂ፣ የአቡጃ የሴፍቲ እና ኤር ናቪጌሽን ግቦችን እንደገና በመከለስ አፅድቋል።
ኢነርጂን በሚመለከት የአፍሪካ የኢነርጂ ውጤታማነት ስትራቴጂ እና አህጉራዊ የአረንጓዴ ሃይድሮጂን ስትራቴጂን ማፅደቁን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች እና የዘርፉ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡