Fana: At a Speed of Life!

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር 10 ሚሊየን ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር 10 ሚሊየን መድረሱን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡

የፕሮግራሙ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አቤኔዘር ፈለቀ እንደገለጹት÷ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሁሉን አቀፍ፣ አካታችና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት ያስችላል፡፡

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አሰራር ሥርዓት በማዘመንና ዲጂታል በማድረግ ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ዲጂታል መታወቂያ በተለያዩ ተቋማት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷በቀጣይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መታወቂያውን እንደ ቅድመ ሁኔታ እንደሚጠይቁ አንስተዋል፡፡

በቅርቡም በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ የባንክ አካውንት ለመክፈት ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን እንደቅድመ ሁኔታ መጠየቅ እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በመዲናዋ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን መያዝ አስገዳጅ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ድረስም 10 ሚሊየን በላይ ዜጎች ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን እንደወሰዱ ነው አቶ አቤኔዘር ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የገለጹት፡፡

ስለሆነም ዜጎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የተለያዩ ማዕከላት ተመዝግበው ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን እንዲያገኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.