አየር ወለድ ጥምር ጀግንነትን የሚጠይቅ የላቀ ወታደራዊ ሙያ ነው – ብ/ጄ ከማል ኤቢሶ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ አየር ወለድ ት/ቤት ብቁ አየር ወለዶችን በማፍራት ረገድ የሚጠበቅበትን እየተወጣ ነው ሲሉ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ም/አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ከማል ኤቢሶ ተናገሩ፡፡
ብ/ጄ ከማል በቢሾፍቱ አየር ወለድ ት/ቤት የአየር ወለድ ስልጠናን ሲያስጀምሩ እንዳሉት÷ አየር ወለድ የግልና የቡድን ጥምር ጀግንነትን ያቀፈ የላቀ ወታደራዊ ሙያ ነው፡፡
አየር ወለድ ግዳጁን በጠላት ወረዳ ከጀርባ፣ በስተ ግራ ወይም ቀኝ ከአየር በመዝለል በግልም ሆነ በቡድን የሚፈጸም በመሆኑ በስልጠና ወቅት ይህንን የሚመጥን ብቃት መላበስ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ማሰልጠኛ ማዕከሉ ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመታገዝ ብቁ አየር ወለዶችን የማፍራት የረጅም ጊዜ ልምድ እንዳለው አስታውሰው፤ ሰልጣኞች ከባዱን የአየር ወለድ ስልጠና በጽናት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ኮሎኔል ቦጃ አጋ በበኩላቸው÷ ት/ቤቱ በርካታ የሀገር ባለውለታ ጀግና አየር ወለዶችን ማፍራቱን ተናግረዋል።
አንድ ሰው አየር ወለድ ለመሆን ከኮማንዶ ስልጠና ጀምሮ በከባድና ፈታኝ የስልጠና ሒደት ውስጥ እንደሚያልፍ አውስተዋል፡፡
ባላቸው ብቃት በመታገዝ የሀገር አልኝታ የሆኑ ሀገርን የሚያሻግሩ እና ሙያዊ ብቃት ያላቸው አየር ወለዶችን ለማብቃት ጠንክረው እንደሚሰሩ መናገራቸውንም የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡