የሰላም አማራጭን መቀበል አዋቂነት ነው- ጃል ሰኚ ነጋሳ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም አማራጭን መቀበል ብልህነትና አዋቂነት መሆኑን በመገንዘብ በጫካ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት የመንግሥትን ጥሪ እንዲቀበሉ የሠራዊቱ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጃል ሰኚ ነጋሳ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ÷ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጋር ያደረጉትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ለተደረገላቸው አቀባበል ሕዝብና መንግሥትን አመሥግነዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ ከተሞችን በጎበኙበት ጊዜ የተመለከቷቸው የልማት ሥራዎችና የከተሞች መነቃቃት እንዳስደነቃቸውም አንስተዋል፡፡
የሰላም ጥሪውን የተቀበሉትም የሕዝብና የመንግሥትን ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች ተከትሎ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እና የሰላም አማራጭን መቀበል ብልህነትና አዋቂነት መሆኑን በመረዳታቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እውነቱ የሰላም መንገድ አማራጭ የሌለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሆኖ ሳለ÷ ስምምነቱ የክልሉን ሰላም የማያረጋግጥ ነው ብለው የተሳሳተ መረጃ የሚያጋሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጅ እነዚህ አካላት የላኪዎቻቸውን ፍላጎት በፕሮፓጋንዳ ለማሟላት የሚፍጨረጨሩ፣ ስለ ጦርነት የማያውቁ፣ በክልሉ የደረሰውን ውድመት የማይረዱ እና የእናቶችን እምባ ለማቆም የማይሹ ናቸው ብለዋል።
በአጠቃላይ እነዚህ አካላት በተለያዩ ሀገራት በምቾት ያሉና በሰው እጅ እሳት መጨበጥ የሚፈልጉ ናቸው ሲሉ ጃል ሰኚ ረጋሳ ተናግረዋል።
እነዚህ ኃይሎች የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ሊያደፈርሱ ቢጥሩም ሳይሳካለቸው ቀርቷል ነው ያሉት፡፡
የተደረሰው ስምምነት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተተገበረ መሆኑን አንስተው÷ ይህ እንዲሳካ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ የኦሮሞ ሕዝብ፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ጥሪውን የተቀበሉ ወዳጆቻቸውን አመስግነዋል፡፡
ሌሎች በጫካ ያሉ የቡድኑ አባላትና የትግል ጓዶቻቸው ቆም ብለው የሕዝቡን ጉዳት በመመልከት እየቀረበ ያለውን የሠላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጠይቀዋል፡፡
በመራኦል ከድር