የባንኮች ተቆጣጣሪ ነኝ ሥራ አስቀጥራለሁ በሚል ከግለሰቦች ገንዘብ በመቀበል የተከሰሰው በ13 ዓመት እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ ባንኮች ተቆጣጣሪ ነኝ በማለት ለስራ ማስቀጠሪያ በሚል ከ11 ግለሰቦች ገንዘብ የተቀበለው ተከሳሽ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የቢሾፍቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ ቢሾፍቱ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ የድለላ ስራ በሚሰራው ፀጋ ስዩም መንገሻ ላይ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 28 ንዑስ ቁጥር 3ን ጠቅሶ ስድስት ክሶች አቅርቦበታል።
በዚህም ተከሳሹ በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ወራቶችና ቀናቶች በቢሾፍቱ ከተማ በማዘጋጃ ቤት አካባቢና በሌሎችም የተለያዩ ስፍራዎች የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ፣ የአቢሲኒያ፣ የአባይና የፀሀይ ባንኮች “ተቆጣጣሪ ነኝ” በማለት 11 ግለሰቦችን በመተዋወቅ በተጠቀሱ ባንኮች በተለያየ ደረጃ ማስቀጠር እንደሚችል ገልጾ በማሳመን በተለያዩ መጠኖች ከግል ተበዳዮቹ ጉዳይ ማስፈጸሚያ አጠቃላይ 381 ሺህ ብር በስሙ በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ሲቀበል እንደነበር ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ ክስ አቅርቦበታል።
ተከሳሹ ችሎት ቀርቦ ክሱ ከተደረሰው በኋላ በክሱ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ፤ ዐቃቤ ሕግ የግል ተበዳዮችን 11 የሰው ምስክርና በአባሪነት የሰነድ ማስረጃ አቅርቦበታል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከል በሰጠው ብይን ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየቶችን መርምሮ ተከሳሹን በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በ9 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ