በወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ሴት ነጋዴዎች የምርቶች ማስተዋወቂያ አውደ ርዕይ አካሄዱ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ሴት ነጋዴዎች በኬንያ የመጀመሪያውን የወጪ ንግድ ምርቶች ማስተዋወቂያ አውደ ርዕይ አካሂደዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ መርሐ-ግብር ላይ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ፈጥሯል።
በመሆኑም ይህንን ዕድል በመጠቀም ኬንያውያን ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በማኀበረሰብ ልማት ውስጥ የሴቶች ሚና ወሳኝ ገልጸው፤ በወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በኬንያ የኢትዮጵያን ምርቶች ለማስተዋወቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።
በአውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን የወጪ ምርት ያስተዋወቁ ኢትዮጵያውያን ሴት ነጋዴዎች በበኩላቸው ኤምባሲው እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።