ሩሲያ የኦርሺኒክ ሚሳኤልን ለቤላሩስ እንደምታስታጥቅ አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሩሲያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችውን የመካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ኦርሺኒክ ሚሳኤል ለጎረቤቷ ቤላሩስ ልታስታጥቅ እንደሆነ አስታወቀች።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቤላሩሱ አቻቸው አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ጋር በሜነስክ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ፕሬዚዳንት ፑቲን÷ አዲሱ የኦርሽኒክ ሚሳኤል በቤላሩስ ግዛት እንደሚሰማራ ጠቅሰው፤ በተመሳሳይ የሩሲያ የሚሳኤል ሃይሎች በቤላሩስ ተሰማርተው የሚሳኤል የተከላ ሂደትን እንደሚመሩ አስታውቀዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2025 አጋማሽ ላይ የኦርሽኒክ ሚሳኤል ስፍራ በመያዝ ዝግጁነቱ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል፡፡
የቤላሩስ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ በበኩላቸው÷ ሩሲያ ቀደም ሲል የኑክሌር ሀይሏን ወደ ሀገራቸው ማስገባቷን አስታውሰው፤ አዲሱ የኦርሺኒክ ሚሳኤል በአጭር ጊዜ ውስጥ በሀገራቸው ውስጥ እንዲሰማራ ጠይቀዋል፡፡
ቤላሩስ አዲሱ ሚሳኤል የሚሰማራበት ስትራቴጂክ ቦታ አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ሚሳኤሉ የሚሰፍርባቸው ቦታዎች በሩሲያ እና ቤላሩስ ወታደራዊ-ፖለቲካዊ አመራር እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡
የመካከለኛ እርቀት ሚሳኤል የሆነው ኦርሺኒክ በቅርቡ ሙከራ ላይ ዋለ ሲሆን ፕሬዚዳንት ፑቲን ኬቭ በሩሲያ ላይ ለምትፈፅመው ጥቃት አፀፋ ለመስጠት ሚሳኤሉን እንደሚጠቀሙበት ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡