ነዋሪነታቸውን በጣሊያን ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ለህዳሴ ግድቡ የ65 ሺህ ዩሮ ቦንድ ግዥ ፈጸሙ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነዋሪነታቸውን በጣሊያን ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ65 ሺህ ዩሮ ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ ለግድቡ ግንባታ የቦንድ ግዥ በመፈጸም ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው።
አሁንም በፍጻሜ ዋዜማ ላይ የሚገኘው ግድቡ እንዲጠናቀቅ አሻራቸውን ለማሳረፍ በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው የ65 ሺህ ዩሮ የቦንድ ግዢ ፈጽመዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የልማት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የአንድነት ተምሳሌት እና የሉዓላዊነት ምልክት በመሆኑ ቦንድ መግዛት እንደ አንድ ዜጋ የሚጠበቅ አኩሪ ተግባር መሆኑን ግለሰቡ ገልጸዋል።
የቦንድ ግዢውን በአካል ተገኝተው በመፈጸም የሀገር ባለ ውለታ ለሆኑት ግለሰብ ኤምባሲው ምስጋናውን አቅርቧል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ97 ነጥብ 6 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ ትልቅ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ፈጥሯል፡፡
አሁን ላይ አራት ተርባይኖች በድምሩ 1 ሺህ 443 ሜ.ዋ ኃይል እንዲያመነጩ መደረጉም ይታወቃል።