Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ሥርዓት የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይጨምራል – አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ሥርዓት የመግባባት ዴሞክራሲን በማንበር የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይጨምራል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

19ኛው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በማስመልከት በአርባምንጭ ከተማ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ባስተላለፉት መልዕክት፤ ብዝኀ ማንነቶች እንደጡብ በታነጹባት ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተጋምደው ሀገር ሲገነቡ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን በማለት አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮቻቸው ላይ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር በመቻላቸው ነው ብለዋል፡፡

የሀገረ መንግሥት ግንባታው ሂደት በየዘመኑ ሲጀመር ሲፈርስ፣ ሲወድቅ ሲነሳ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን የተጀመረው የሀገረ መንግሥት ግንባታ በስኬት እንዲጓዝ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ፌዴራሊዝም በስምምነትና በመተማመን በአንድነት ለመኖር የሚያስችል የሕግ ተጠያቂነት ያለው ሥርዓት ነው በማለት ገልጸው፤ ፌዴራሊዝም ችግሮች ሲያጋጥሙት በንግግር መፍታት የሚያስችል መተማመንን፣ መደጋገፍንና መተባበርን መሠረት የሚያደርግ ፍልስፍና ነው ብለዋል።

የፌዴራል ሥርዓት ሁልጊዜም ፍቃደኝነትን፣ ስምምነትንና ውዴታን በመጠየቅና በማረጋገጥ ሀገራዊ መግባባትና ኅብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ተስማምተን የምናስቀጥለው ሥርዓት ዘላቂ ሰላም፣ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገትና በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስር ለመገንባት እድል የሚፈጥር ሆኖ ይገኛል ብለዋል።

የፌዴራል ሥርዓት የመግባባት ዲሞክራሲን በማንበር የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ይጨምራል፤ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱም እንዲጎለብት ያደርጋል በማለት ገልጸዋል።

ይህም የሀገረ መንግሥት ግንባታው ሂደት ጥንካሬውን እያሰፋ ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ ተቋማትና የተረጋጋ ሀገር ለማስረከብ ያስችላል ብለዋል፡፡

በዙፋን ካሳሁን እና ወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.