እንደ አርባምንጭ ያሉ ከተሞችን እድገት መመልከት ሁልጊዜም አስደሳች ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ደቡብ ኢትዮጵያን መጎብኘት እና እንደአርባምንጭ ያሉ ከተሞችን እድገት መመልከት ሁልጊዜም አስደሳች ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ደቡብ ኢትዮጵያን መጎብኘት እና እንደአርባምንጭ ያሉ ከተሞችን እድገት መመልከት ሁልጊዜም አስደሳች ነው ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ለከተሞችም ሆነ ለገጠር አካባቢዎች ፈተና ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ዛሬ በመጎብኘት ላይ እንዳለነው አይነት የሙዝ ልማት ሥራዎችን በገጠር አካባቢዎች በማሳዎች ላይ የኩታ ገጠም እርሻ አሰራረን ጀምረናል ነው ያሉት፡፡
እነዚህን ጥረቶች የሚደግፈው የሌማት ትሩፋት ሥራ በየአርሶ እና አርብቶ አደሩ ቤት የእንቁላል ምርትን ከአሳ እና ከብት እርባታ ብሎም ንብ ማነብ ጋር ምርት በማሳደግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
መርሃ ግብሮቹ በጥምር የገጠሩ እና የከተማው ነዋሪዎች ከትሩፋቱ እንዲካፈሉ አልመው ሰርተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷በተለይ የኩታ ገጠም እርሻ በአርባ ምንጭ ታላቅ ተስፋ የሰነቀ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡