በኮሩ የምስረታ ቀን በመስዋዕትነት የፀናውን ሀገር ለመጠበቅ ዳግም ቃል መግባት እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኮሩ የምስረታ ቀን መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን መዘከርና በመስዋዕትነት የፀናውን ሀገር ለመጠበቅ ዳግም ቃል መግባት እንደሚገባ ተገለፀ።
የተወርዋሪ ኮከብ ኮር የሶስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩ ቀጥሏል።
የኮሩን አመሠራረት በሚመለከት በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የኮሩ አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ÷ በዓሉን ስናከብር የጀግኖችን መስዋዕትነት እየዘከርንና ለሀገራችን የገባነውን ቃል ኪዳን ለማደስ ዳግም ቃል በመግባት ይሆናል ብለዋል፡፡
ኮሩ በአስቸጋሪ ወቅት ቀድሞ በመድረስ ውድ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈል ሀገራቸውን ያፀኑ ጀግኖችን እያፈራ መቆየቱን አውስተው የጀግኖችን አደራ ለማስቀጠል እየተሰራ እንደሚገኝም መግለፃቸውን የመከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ ትስስር ገፅ መረጃ ያመላክታል፡፡
በመርሐግብሩ የደቡብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሰለሞን ኢተፋ ፣ የሜካናይዝድ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ከፍያለው አምዴ፣ የመከላከያ ሠራዊት የሥነ ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳንና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡