ክልሉን የሰላምና የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሆን እንሰራለን- አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሆን አበክረን እንሰራለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ነገ የሚከበረውን የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማስመልከት በአርባ ምንጭ ከተማ ደማቅ የዋዜማ ምሽት እንዲሁም የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ አቶ ጥላሁን ከበደ÷ ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት በሚል መሪ ሃሳብ ለ 19ኛ ጊዜ ለሚከበረው በዓል ወደ ክልሉ ለመጡ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከ6ቱ የክልል ማዕከላት አንዷ የሆነችው አርባ ምንጭ ከተማ የሚገባትን ያህል እድገት ባታስመዘግብም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሁሉም ልብ የሚጣልባት ከተማ እንድትሆን ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።
የብልፅግና ትሩፋት የሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሆን የክልሉ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ክልሉ የብሄራዊነት ትርክት የጎላበት እንዲሆን እና ለዘመናት ሲቀነቀን የቆየው የነጠላ ትርክት ያመጣውን የከፋፋይነት እሳቤ ለመሻር እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሉ በዓሉን እንዲያዘጋጅ ለሰጠው ዕድል ምስጋና አቅርበዋል።