በመላ ሀገሪቱ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል ወደነበረበት ተመለሰ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በመላ ሀገሪቱ በሲስተም አለመረጋጋት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ሃይል ወደነበረበት መመለሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው የሃይል መቋረጥ ወደነበረበት ተመልሷል፡፡
በመላው ሀገሪቱ ተቋርጦ የነበረውን የኤሌክትሪክ ሃይል ወደነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን አንስተዋል፡፡
የሲስተሙን ቮልቴጅ በማረጋጋት የተቋረጠውን ሃይል ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የሚያስችል ሥራ መከናወኑንም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የተፈጠረው ችግር እስኪፈታ ድረስ በትዕግስት ለጠበቁ ደንበኞች ምስጋና አቅርቧል።
በመላኩ ገድፍ