ከለውጡ ወዲህ በሕዝቦች መካከል ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠነክሩ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል- አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ ወዲህ በህዝቦች መካከል ከልዩት ይልቅ አንድነትን ሊያጠነክሩ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ተከበረ።
በአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ፣ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የሕዝብ ተወካዮቸ ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ተገኝተዋል፡፡
እንዲሁም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዓሉ ታድመዋል፡፡
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በበዓሉ አከባበር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ምክር ቤቱ ጤናማ የፌዴራል ስርዓት እንዲጎለብት በርካታ ስራዎች እየሰራ ቆይቷል፤አሁንም እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተያዘውን ሀገራዊ አንድነት የመገንባት ተልእኮ ለመወጣት በሰተራው ስራ ተጨባጭ ውጤቶች መታየት መጀመራቸውንም አንስተዋል፡፡
ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት የሚያስችል የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራበት መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ በተሰራው በርካታ ስራ በህዝቦች መካከል ከልዩት ይልቅ አንድነትን የሚያጠነክሩ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት አፈ ጉባዔው ፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው