ጠንካራና የታፈረች ህብረ ብሔራዊት ሀገር ለመገንባት በጋራ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይገባል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አንድነት የሚገለጥባት ድንቅ ምድር ናት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም የብሔር ብሔረሰቦች ኅብር የኢትዮጵያን አንድነት አይሸረሽረውም፤ ሀገራዊ አንድነቷ ኅብራዊነቷን አይጠቀልለውም፤ ሁለቱም ያስፈልጓታል ሲሉ ብለዋል።
ኅብራዊነቷ ጌጧ፣ መልኳ፣ ጸጋዋ፣ ሃብቷ ነው፤ አንድነቷ ደግሞ ኃይሏ፣ ጉልበቷ፣ አቅሟ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ስናከብር የኢትዮጵያን ቀለመ ብዙ ማንነት፣ እሴትና ፀጋ በማውሳት መሆን እንዳለበት አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኅብር ናት ፤አንድነት የሚገለጥባት ድንቅ ምድር ናት ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡፡
ሆኖም ዛሬም ነጠላ ትርክት የወለደው የፖለቲካ ስብራት እንዲሁም ድህነት የሀገራችንን የከፍታ ጉዞ ወደ ኋላ መጎተቱ አልቀረም ነው ያሉት፡፡
እነዚህን ሳንካዎች በማለፍ የበለፀገች፣ ጠንካራና የታፈረች ህብረ ብሔራዊት ሀገር ለመገንባት በጋራ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉትን እምቅ ጥበብ፣ እውቀት፣ ሀገር አሻጋሪ ሀሳቦችና ባህሎች በመደመር ለሀገር የከፍታ ጉዞ እና ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠቀም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል ።
መግባባት ስንፈጥር የተደመረ አቅም ይኖረናል፤ ይህ ደግሞ ከልዩነት ፖለቲካ ወደ አንድነት ከድህነት ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ ያፋጥናል ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡