ኢትዮጵያ የኖትርዳም ጎቲክ ካቴድራል ዳግም ለአገልግሎት ክፍት በመሆኑ መልካም ምኞቷን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአምስት ዓመታት በፊት በቀጣሎ ጉዳት ደርሶበት ጥገና ሲደረግለት የነበረው ጥንታዊው የካቶሊክ ቤተ-ዕምነት የሆነው ኖትርዳም ጎቲክ ካቴድራል ጥገና ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
እድሳቱ ተጠናቅቆ ዳግም ወደ አገልግሎት መመለሱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ለፈረንሳይ መንግሥት እና ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
በመልዕክቷም÷ የበርካታ ዜጎችን ቀልብ የሚይዘው ጥንታዊው የኖተርዳም ካቴድራል ከአምስት ዓመታት በላይ ሲታደስ ቆይቶ በይበልጥ ሳቢ እንዲሆን ተደርጎ መሠራቱን ጠቅሳለች፡፡
በዚህም ፈረንሳይ ለቅርስ ያላትን ቁርጠኝነትን ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ እና ባለሃብቱ ኤለን መስክን ጨምሮ ከ1 ሺህ 500 በላይ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት የኖትርዳም ጎቲክ ካቴድራል ትናንት ዳግም ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወሳል፡፡
ካቴድራሉ በፈረንጆቹ ከ1991 ጀምሮም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሣይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ይታወቃል፡፡