እስከ አሁን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ ገቢ ለማሰባሰብ በሶማሌ ክልል የነበረውን የአንድ ዓመት ቆይታ በማጠናቀቅ ዛሬ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተላልፏል፡፡
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ተገኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ዋንጫው በሶማሌ ክልል ቆይታው ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ እስከ አሁን ከሕዝብ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተጠቁሟል፡፡
በያዝነው የበጀት ዓመት ባለፉት አራት ወራትም ከ311 ሚሊየን ብር በላይ ከሕዝብ መሰብሰቡን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት 97 ነጥብ 6 በመቶ ተጠናቅቋል ተብሏል፡፡