Fana: At a Speed of Life!

ቼክ ሪፐብሊክ በግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቼክ ሪፐብሊክ በግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት እና በእንስሳት ልማት ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋገጠች፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያን ጁርካ ጋር በትብብር በሚሠሩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት፤ በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ ዐሻራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል፡፡

ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማጎልበት በግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ከቼክ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ትፈልጋለች ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ማሪያን ጁርካ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን አድንቀው÷ በግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት እና በእንስሳት ልማት ዘርፎች በትብብር ለመሥራት የሀገራቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ የቼክ ሪፐብሊክ ልዑክ በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቅጥር ጊቢ ያሉ የእርሻ መሣሪያዎች፣ ትራክተሮችን እና የመገጣጠሚያ ማዕከላትን ጎብኝቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.