Fana: At a Speed of Life!

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የተሰማሩ ባለሃብቶች በተኪ ምርት ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባሕር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ የተሰማሩ ባለሃብቶች የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ተኪ ምርት በማምረት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የባሕርዳር ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጥሩዬ ቁሜ÷ በፓርኩ ባለሃብቶች በአግሮ ፕሮሰሲንግና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች መሰማራታቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማስፋት፣ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት፣ ለአርሶ አደሩ ምርት የገበያ ትስስር በማመቻቸትና የስራ እድል በመፍጠር ለኢኮኖሚው እድገት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በትራንስፎርመር ማምረትና በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ አምስት ባለሃብቶች በስራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙና ተኪ ምርት የሚያመርቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ፣ የተደራጀ ዳታ ቤዝና ደህንነቱን የሚያስጠብቅ የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት መሆኑንም አስረድተዋል።

እንዲሁም የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ስርዓት የተገነባለት፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በፓርኩ ሶስት ሼዶችና 96 ሄክታር መሬት ያልተያዘ እንዳለ አንስተው÷ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ፓርኩ በመምጣት ወደ ልማት እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.