የሰው ህይወትን ለማሻሻል ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው – ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ህይወትን ለማሻሻል እና የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዛሬ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር በመመረቅ ከካዛንቺስ በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች አስረክበናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መልክ የሆነችው አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ መሰረተ ልማት ከማሟላት በተጨማሪ የሰው ህይወትን ለማሻሻልና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ነዋሪዎችን ካረጀና ለመኖር ምቹ ካልሆነ የካዛንቺስ አካባቢ እንዲወጡ በማድረግ ለኑሮ ምቹ የሆነ ቤትና አካባቢ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸው፥ በዚህም የሰው ህይወትን የመቀየር ስራን ሰርተናል ብለዋል።
ከካዛንቺስ አካባቢ ለልማት በፈቃደኝነት የተነሳችሁ እና ከጎናችን የቆማችሁ ነዋሪዎችን ስለ ትዕግስታችሁ እና ድጋፋችሁ አመስግናለሁ ያሉ ሲሆን፥ ለስራው ቦታውን በፈቃደኝነት ለልማት የለቀቁ የአካባቢው አርሶ አደሮችንም አመስግነዋል፡፡
ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተው ያጠናቀቁ ኮንትራክተሮችን፣ አማካሪ ድርጅቶችን፣ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን፣ ያስተባበሩ አመራሮችንም አመስግነዋል፡፡