ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ኢንሼቲቭ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ኢንሼቲቭ እና አረንጓዴ ልማት ድጋፍ እንደምታደርግ የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ኒኮላይ ዋመን ገለጹ፡፡
ኒኮላይ ዋመን ከኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ ዘርፎች የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጎልበት መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ29) ወቅት ኢትዮጵያና ዴንማርክ ትብብራቸውን እንዳሳዩ አስታውሰው፤ ይህም ሀገራቱ በቀጣይ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩ ያመለክታል ብለዋል፡፡
የሀገራቱ በአየር ንብረት ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ጠቅሰው፤ በአረንጓዴ ልማት በአፍሪካ መሪ ተዋናይ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ሀገራቸው በትብብር መስራቷ አስደሳች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትተገብረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በአብነት እንደሚጠቀስ ገልጸው፤ ዴንማርክ በቀጣይ አመታት ለአረንጓዴ ኢኒሼቲቭ 200 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ተማሪዎችን ጨምሮ ህዝብን በማሳተፍ ለምታካሂደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቁመዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ጫና ለመቀነስ በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ውጤቱ የጋራ ነው ብለዋል፡፡
ዴንማርክ ለአየር ንብረት ለውጥ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ረገድ በቀዳሚነትና በአረአያነት እንደምትነሳ ገልጸው፤ ሁሉም አካላት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ