ከ132 ሚሊየን ብር በላይ በታክስ ማጭበርበር የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ132 ሚሊየን ብር በላይ በታክስ ማጭበርበርና መሰወር የተጠረጠሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አብዱሰላም መሃመድ÷ሕግን ለማስከበር በተሰራው ሥራ በታክስ ማጭበርበርና መሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የታክስ ማጭበርበርና መሰወር ወንጀል መፈፀማቸው በኦዲት የተደረሰባቸው ግለሰቦች በወንጀል ምርመራ በኩል ምርመራ ተደርጐባቸው እንዲከሰሱ የተላለፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በታክስ አስተዳደር አዋጅ ሕግ መሰረት የተጭበረበረና ሀሰተኛ ግብይት የተፈጸመባቸው ሂሳባቸው ውድቅ ተደርጎ እንደገና እየተሰራ መሆኑንና በቀጣይ በሕግ የሚጠየቁበት ሂደት መኖሩ ተጠቁሟል፡፡
ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል 132 ሚሊየን 443 ሺህ 47 ብር በተቋሙና በመንግስት ገቢ ላይ ጉዳት ማድረሱንም የአስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡