Fana: At a Speed of Life!

ከ25 ቢሊየን ብር በላይ የግብር ታክስ ጉዳት ያደረሰው ተከሳሽ በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ25 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የግብር ታክስ ጉዳት አድርሷል ተብሎ ክስ የቀረበበት በረከት አለኸኝ በ10 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ወሰነ።

የፍትህ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ላይ በነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም በሀሰተኛ ሰነድ የባንክ ሒሳብ መክፈት፣ በህገወጥ መንገድ ንግድ ፍቃድ ማውጣትና ማደስ፣ የታክስ አዋጁን መተላለፍ፣ ሀሰተኛ ሰነዶችን መጠቀም፣ የገቢ ደረሰኞችን አትሞ ለተለያዩ ነጋዴዎች ማሰራጨት የሚል ተደራራቢ 7 ክሶች በዝርዝር ማቅረቡ ይታወሳል።

በተለይም በመስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም እና በመስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም ፍቃድ በማሳደስ የተመዘገበዉ በአስመጪነት ንግድ ስራ ዘርፍ ሆኖ ሳለ ምንም አይነት እቃ ከዉጭ ሀገር ሳያስገባ እና የሀገር ዉስጥ የዕቃ ግዥ ሳይፈጽም ከወሰደው የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ደረሰኞችን በማተም ለ339 ግብር ከፋዮች 1 ሺህ 663 ደረሰኞችን በማሰራጨት በ15 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ 25 ቢሊየን 989 ሚሊየን 943 ሺህ 223 ብር ከ83 ሳንቲም ጉዳት ደርሷል በማለት ዐቃቤ ሕግ ካቀረባቸው ክሶች መካከል ጠቅሶ ነበር።

ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ 30 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል በማለት ያቀረበው ዝርዝር ክስ ለተከሳሽ ከደረሰው በኋላ ግለሰቡ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸሙን ጠቅሶ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ ዐቃቤ ህግ 13 የሰው ምስክሮችን እና 23 ገላጭና አስረጂ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ የተሰሙ የሰው ምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ሰጥቶም ነበር።

በዚህም ፍርድ ቤቱ በአንደኛና በሁለተኛ ክሶች ላይ ማለትም ሰለሞን ሙሉ ከውል በሚል የፈጠራ ስም በወጣ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያና ሀሰተኛ ውክልና መሰረት የንግድ ፍቃድ በማውጣትና በማሳደስ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ተብሎ የቀረበውን ክስ በሚመለከት፣ ንግድ ፍቃድ መውጣቱንና መታደሱን እንጂ ሰለሞን ሙሉ ከውን በተባለው ሰው ወይም በተወካይ ንግድ ቢሮ ቀርቦ ንግድ ፍቃዱን ማን አወጣ ማን አሳደሰ የሚለው አሳማኝ ማረጋገጫ ያልቀረበ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አብራርቷል።

በተጨማሪም ከምስክሮች ቃል አሰጣጥ አንጻር በሰነዶች ማረጋጋጫ ተቋም አንድ ሰው በአካል ሳይቀርብ የጣት አሻራ ሳይሰጥና ሳይፈርም ውክልና እንደማይሰጥ መረዳቱን በመጥቀስ ሰለሞን ሙሉ ከውን በሚባል ሰው አሻራ ሰጥቶ ፈርሞ፣ በአካል ቀርቦ ውክልና የሰጠና ንግድ ፍቃድም ያወጣና ያሳደሰ መሆኑን ግምት መያዙን በማብራራት ከ1ኛ እና ከ2ኛ ክስ ነጻ ብሎታል።

ፍርድ ቤቱ 3ኛ እና 4ኛ ክስን በሚመለከት በ2010 እና በ2011 ዓ.ም ከውጭ ሀገር እቃ ሳያስገባና ምንም አይነት ሽያጭ ሳያከናውን ሀሰተኛ የተጭበረበሩ ሰነዶችን የዓመታዊ የግብር ሪፖርትን ለግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ማስገባቱ መረጋገጡን በመጥቀስ 3ኛ ክስ ከ4ኛ ክስ ጋር ተጠቃሎ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ለ339 ግብር ከፋዮች 1 ሺህ 663 የገቢ ደረሰኞችን አትሞ በማሰራጨት የንግድ ትርፍና የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በ15 የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ 25 ቢሊየን 989 ሚሊየን 943 ሺህ 223 ብር ከ83 ሳንቲም ጉዳት መድረሱን በማስረጃ መረጋገጡን ገልጾ፤ 5ኛ ክስን ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።

6ኛ ክስን በሚመለከት ደግሞ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በተከራየው ሱቅ ውስጥ ህገወጥ እውቅና የሌለው የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያና ኮምፒዩተሮች በገቢዎች ሰራተኞች ተገኝቷል ተብሎ የቀረበው ክስን በሚመለከት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያው ከጁፒተር ንግድ ስራዎች ድርጅት የተገዛና የተገጠመ መሆኑን መረጋገጡን ችሎቱ ጠቅሶ እውቅና የሌለው ህገወጥ መሳሪያ ተገኝቷል በሚል በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ክስን በሚመለከት ግን ማስረጃ አለመቅረቡን ገልጾ፥ ተከሳሹን በ6ኛ ክስ ነጻ ነው ብሎታል።

7ኛ ክስን በሚመለከት የታክስ አስተዳደር አዋጅን በመተላለፍ ግብይት ሳይኖር ህገወጥ ደረሰኝ መጠቀም የሚለው ክስ ከ5ኛ ክስ ዝርዝር ጋር በተመሳሳይ በሀሳብ መደራረብ ያለው መሆኑን ጠቅሶ፤ ፍርድ ቤቱ 7ኛ ክስን በሚመለከት ነጻ በማለት ብይን ሰጥቷል።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረበውን የመከላከያ ማስረጃ መርምሮና ከዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ጋር አመዛዝኖ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ማረጋገጡን ጠቅሶ በሙሉ ጥፋተኛ ብሎታል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ ቅጣት አስተያየት መርምሮ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ተከሳሹ ያቀረበውን 5 የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በእርከን 29 መሰረት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ3 ሚሊየን 8 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.