ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላት የሃይል ትስስር በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በኬንያ እየተካሄደ በሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡፡
ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በዚህ ወቅት ÷ በሀገራት መካከል የሚደረግ የሃይል ትስስር በየሀገራቱ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣናው የሚፈጠረው የሃይል ትስስር የታዳሽ ሃይል ልማትን በስፋት ለማከናወንና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ንጹህ ኢነርጂን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ የሃይል ትስስሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ነው ያስረዱት፡፡
በመድረኩ የተገኙ የዓለም ባንክና ሌሎች የልማት አጋር ድርጅቶች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እያከናወነች የሚገኘው የሃይል ትስስር ለሌሎች አካባቢዎች ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር በፈረንጆቹ 2025 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ሙሉ በሙሉ ሥራ እንደሚጀምር በአባል ሀገራት መካከል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ኬንያ እና ሱዳን ሃይል በማቅረብ ላይ የምትገኝ ሲሆን÷በቀጣይም ለደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ ሃይል ለማቅረብ በሒደት ላይ መሆኗን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡