ዲሽታ ጊና የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደጋገፍ እሴቶችን ያቀፉ በዓል ነው – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለአሪ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ ዲሽታ ጊና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ዲሽታ ጊና የአሪ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ፤ በብሄሩ የጊዜ ቀመር በወርሃ ታህሳስ መጀመሪያ ላይ በድምቀት የሚከበር ድንቅ የክልሉ እሴት ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ በብሔረሰቡ ባህልና ትውፊት መሠረት፣ አዝመራው አሽቶና ፍሬ አፍርቶ በሚቀመስበትና ብሩህ ተስፋን በሚፈነጥቅበት ወቅት የሚከበር፣ አስቸጋሪው ወቅት ማለፉን በማብሰር ብሩህ ዘመንን በአዲስ መንፈስ በፍቅር የሚቀበሉበት መሆኑንም አንስተዋል።
የተራራቁና የተነፋፈቁ የሚገናኙበትና የተጣሉ ይቅር የሚባባሉበት በዓሉ÷ የአሪ ህዝብ ዓመቱ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ምኞትና ምስጋና ለፈጣሪ የሚያደርስበት የምስጋና በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የሚከበረው ዲሽታ ጊና በአንድነት የሚያከብረው ልዩና የማንነቱ መገለጫ የሆነ የሰላም፣ የአብሮነት፣የመተሳሰብ እና የወንድማማችነት ተምሳሌት እንደሆነም አውስተዋል፡፡
በዓሉ ሌሎች ወንድም እህት ህዝቦች ጋር በአብሮነትና በአንድነት፣ የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጠናክር እና የወንድማማችነት እሴቶችን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል ነው ያሉት።
ዲሽታ ጊና የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደጋገፍ እሴቶችን ባቀፉ ባህላዊ ክዋኔዎች የታጀበ በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም አባቶች ያቆዩትን ይህን ድንቅ እሴት የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት በዓሉን ከነሙሉ ባህላዊ እሴቱና ትውፊቱ ጠብቆ ማቆየትና ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር መስራት ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪ የበዓሉን አከባበር በማስተዋወቅና በማጎልበት በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማሳደግ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የአብሮነት እንዲሆን መመኘታቸውንም የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡