Fana: At a Speed of Life!

የዋይ ኤም ጂ ጎልድ ማይኒንግ ተቋም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተስፋ ሰጪ እድሎችን ይዞ የመጣ ሆኗል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሻኪሶ በቅርቡ የተመረቀው የዋይ ኤም ጂ ጎልድ ማይኒንግ ተቋም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተስፋ ሰጪ እድሎችን ይዞ የመጣ ሆኗል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋይ ኤም ጂ ጎልድ ማይኒንግ ተቋም እና የሚድሮክ ጎልድ የሥራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዕድሎች ማሳያ የሆነች በአህጉሩ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ ናት ብለዋል።

በማደግ ላይ ካሉት ዘርፎቿ መካከል ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ሰፊ አቅም ያለውና እድገቷን በመምራት ትልቅ ስፍራ እየያዘ የመጣው የወርቅ ማምረት ኢንዱስትሪ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በወርቅ ክምችት የታደሉት የሻኪሶ እና ሰፊው የጉጂ አካባቢ የማዕድን ማውጣት ሥራው ዐቢይ ስፍራዎች ናቸው በማለት ገልጸው፤ በሻኪሶ በቅርቡ የተመረቀው የዋይ ኤም ጂ ጎልድ ማይኒንግ ተቋም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ተስፋ ሰጪ እድሎችን ይዞ የመጣ ሆኗል ብለዋል።

በመሬት ስበት ተመሥርቶ የሚሰራውን ዘመናዊ የማዕድን ቴክኖሎጂን የሚጠቀመው የዋይ ኤም ጂ የምርት ሥራ ጠንቀኛ ኬሚካሎችን ከመጠቀም የተጠበቀ ፈጠራ የሞላበት እና የአካባቢ ጥበቃ ተስማሚነትን ያረጋገጠ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በጉጂ ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ መሪ የወርቅ ምርት ኩባንያዎች አንዱ የሆነውን የሚድሮክ ጎልድ የሥራ እንቅስቃሴን የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኩባንያው በትልቅ አቅምና ደረጃ በሚሰራው የወርቅ ምርት ሥራ ለኢትዮጵያ የማዕድን ከባቢ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.