Fana: At a Speed of Life!

ከኤሌክትሪክ መስመር አቅራቢያ ያሉ ዛፎችን የመቁረጥ ሥራ የኃይል መቆራረጥን የመቀነስ ጥረት አካል ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኤሌክትሪክ መስመር በሦስት ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ዛፎችን የመቁረጥ ሥራ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን የመቀነስ ጥረት አካል ነው ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጿል።

የዛፎች ተከላ፣ የቤት፣ አጥር፣ ሕንጻና የመንገድ ግንባታዎች በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ሕግ የተቀመጠውን የርቀት ስታንዳርድ ጠብቀው አለመከናወን ለኃይል መቆራረጥ ዋና መንስዔዎች መሆናቸውንም ገልጿል፡፡

የኃይል መቆራረጥን በጊዜያዊነት ለመቀነስ የማሻሻያ እና የጥገና ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጸው ተቋሙ÷ ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ያለው ከኤሌክትሪክ መስመር በሦስት ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ዛፎችን የመቁረጥ እና የቅድመ ጥገና ሥራ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የኃይል መቆራረጥን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ የኔትወርክ መልሶ ግንባታ እና ማሻሻያ ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በዋና ዋና መስመሮች ላይ እየተከናወኑ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ ትራንስሚሽን እና ዲስትሪቢዩሽን መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት፣ የሥድስቱ ከተሞች መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት እንዲሁም የ10 ከተሞች ዲስትሪቢዩሽን ኔትዎርክ ማሻሻያ ፕሮጀክት ሥራዎችን ጠቅሷል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁም በከተሞቹ የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀርፉ ይጠበቃል ነው ያለው፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.