የዲሽታ ግና በዓል እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ብሔር የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ ዲሽታ ግና በዓል በጂንካ ከተማ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በየዓመቱ የሚከበረው የዲሽታ ግና በዓል ዘንድሮም ‘’ዲሽታ ግና ለሰላም፣ ለአብሮነት እና ለልማት’’ በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡
በዓሉ ከጥንት ጀምሮ እየተከበረ የኖረ መሆኑ ሚታወቅ ሲሆን÷ በዐደባባይ መከበር ከጀመረ ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዓሉ በሕዝቡ ውስጥ ያሉ መልካም እሴቶች የሚንጸባረቁበት ከመሆኑም ባሻገር ለሀገሪቱ ሰላም እና አንድነት የሚጸለይበት ነው መባሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፥ ዲሽታ ግና በኣሪ ብሔር ዘንድ የተጣላ ይቅር የሚሉትና ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት የሚፀለይበትና ከዘመን ዘመን መለወጫ ባሻገር በምድሪቱ ሰላም የሚወርድበት በዓል ነዉ ብለዋል፡፡
ይህን የዲሽታ እሴቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በዓሉ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገሪቱ ብልጽግና ትልቅ አቅም እንደሚሆን አንስተው፥ ክልሉን የብልጽግናና የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩት ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በዓሉን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡