Fana: At a Speed of Life!

ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል – አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለስራ እድል ፈጠራ የተለየ ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

በክልሉ ዋና ዋና የንቅናቄ ተግባራት አፈጻጸም እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የአመራር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፍ የሚተገበሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ሊሆኑ ይገባል።

ገቢ እና የስራ እድል ፈጠራ ከምንም በላይ አስፈላጊ ዘርፎች ናቸው በማለት ገልጸው፤ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን ቀጣይነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢ ማሰባሰብ ካልተቻለ የታቀዱ ተግባራትን ውጤታማ ማድረግ አዳጋች ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በሌላ መልኩ ለስራ እድል ፈጠራ የተለየ ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

በገቢ እና በስራ እድል ፈጠራ ላይ የተስተዋሉ ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እና ውስንነቶችን ፈጥኖ በማረም በዘርፉ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቃል ብለዋል።

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ስራዎችን በዝርዝር በመፈተሽ ለውጤታማነቱ የጋራ ጥረት ማድረግ ተገቢ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ተረጂነትን ለማስወገድ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ዋና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል ሲሉ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.