የምክር ቤት አባላት የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠራቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ትላልቅ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠሩ መሆናቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል፡፡
በስብሰባው የምክር ቤት አባላት ለመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
በዚህም የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉ በመጥቀስ የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ እና እየተገነቡ ባሉ የመስኖ ፕሮጀክት ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ሚኒስቴሩ ምን እየሰራ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
እንዲሁም የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እየፈጠሩ መሆናቸውን አንስተው÷ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉና አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አንጻር እየተሰራ ያለው ስራ እንዲገለጽም ጠቁመዋል፡፡
እንደሀገር ከሪፎርሙ በፊትና ከሪፎርሙ በኋላ በጥናት ተለይተው በበጀትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሳይለሙ የቀሩ የመስኖ የልማት አውታሮችን አልምቶ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ምን ታቅዷልም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ግብርናን ለማዘመን የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑንም በመግለጽ ተቋሙ ቅንጅታዊ አሰራርና ሙያዊ ድጋፍ ከመስጠት አንጻር ምን ደረጃ ላይ ይገኛልም ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
ለእነዚህና ሌሎች የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የሥራ እንቅስቃሴዎች አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ ይዘን እንቀርባለን።
በየሻምበል ምሕረት