Fana: At a Speed of Life!

የመስኖ ፕሮጀክቶች በተቀመጠው የአሰራር ስርዓት መሰረት ብቻ እንዲቀጥሉ እየተሰራ ነው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣይ የሚጀመሩ ሁሉም የመስኖ ፕሮጀክቶች በተቀመጠው ስታንዳርድና የአሰራር ስርዓት መሰረት ብቻ እንዲቀጥሉ እየተሰራ ነው ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን÷ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም÷ ምክር ቤቱ የሚሰጠውን ግብዓት መነሻ በማድረግ ተቋማቸው የያዛቸውን ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ማጠናቀቅ ያልተቻለበትን ምክንያት በመለየት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

እያንዳንዱ ፕሮጀክት ያለበትን ሁኔታና የደረሰበትን ደረጃ ለማየት ሙከራ መደረጉን ገልጸው፤ ችግሮችን ለመለየትና መፍትሔም ለማፈላለግ ግምገማዎች እንደነበሩ፣ ከእያንዳንዱ አማካሪና ሥራ ተቋራጭ ጋር ውይይትና ምክክር መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶች የሚመረጡበት፣ ጥናት የሚጀመርበት እንዲሁም ወደ ተግባር የሚገቡበት ሁኔታን በተመለከተ ግልጽ የሆነ የአሰራር ስርዓት መቅረጽ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው በማለት ገልጸዋል።

የዲዛይንና የግዥ ሂደት ላይ የነበሩ ችግሮን እንዲሁም በግንባታ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የፕሮጀክት ዲዛይን ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያግዙ 30 የሚሆኑ ስታንዳርዶችን ቀርጸናል ብለዋል፡፡

ከዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ)፣ ከአዲስ አበባና ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰው÷ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ሲገቡ የሚያልፉባቸው ስታንዳርዶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ሂደቶችን ሳያልፍ ወደ ኮንስትራክሽን የሚገባ ፕሮጀክት ዲዛይኑ እየተስተካከለ ይቀጥላል ያሉት አብርሃም በላይ (ዶ/ር)÷ በተባለው በጀት ሊሰራ አይችልም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ የሚጀመሩ ሁሉም የመስኖ ፕሮጀክቶች ባስቀመጥነው ስታንዳርድና የአሰራር ስርዓት መሰረት እንዲቀጥሉ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.