በቀጣዮቹ 10 ቀናት የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚቀጥል ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣዮቹ አሥር ቀናት የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለይም በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅ እና በደቡብ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አመላከተ፡፡
ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
በዚሁ ምክንያትም የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይቀጥላል መባሉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
እንዲሁም የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለይም በሰሜን ምሥራቅ፣ በሰሜን፣ በምሥራቅና በደቡብ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀጣይነት እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
በጥቂት የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የደመና ሽፋን የሚኖር ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በምዕራብ፣ በደቡብ ምዕራብ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡