የሕብረተሰቡን የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕብረተሰቡን የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላት ብሔራዊ መርሐ-ግብር ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን የግርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከታንዛኒያ ልዑካን ቡድን ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ቁልፍ ተቋማት መለየታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ለግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና አይሲቲ ዘርፎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ለሀገሪቱ 1/3ኛ አጠቃላይ ዕድገት፣ 2/3ኛ የወጪ ንግድ እንዲሁም 65 በመቶ የሥራ ዕድል ምንጭ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው በማለት ገልጸው፤ የአጋር አካላትንና የፕሮጀክቶችን ድጋፍ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር አንድ ዕቅድና አንድ ሪፖርት እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከገጠሩ ክፍል ባሻገር የከተማ ግብርና ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አንስተው፤ የሕብረተሰቡን የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላት ብሔራዊ መርሐ-ግብር ተቀርጾ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ የወተት፣ ዶሮ፣ ማር እና ዓሣ መንደሮችን በየአካባቢው በመመስረት ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
እነዚህን መንደሮች ማስፋፋት ከውጭ የሚገባውን የዶሮ ስጋ ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ አድንነቀው፤ የሁለትዮሽ ትብብሩ አንዱ ከሌላው ልምድ እንዲቀስም የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉ ሲሆን በእንስሳት ልማቱ የተገኙ ተሞክሮዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡