በመዲናዋ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በተደራጀ የዝርፊያና የስርቆት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
የፀጥታና ደኅንነት አካላት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም የከተማዋን ፀጥታ ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች እንዲሁም በተደራጀ የዝርፊያና የስርቆት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
አሁን ላይ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ሰላምና ደህንነት በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በውይይት መድረኩ የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይም ይህንኑ የሰላም ሁኔታ የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ተቀምጠው የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩና በማንኛውም ሁኔታ ለከተማዋ ፀጥታና ደህንነት ስጋት የሚሆኑ ቡድኖችን ያማከለ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለጹን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።