Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ጽ/ቤት ባለፈው አንድ ዓመት ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያስችለው ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር መስራቱን አስታወቀ።

ጽ/ቤቱ “ከታህሳስ እስከ ታህሳስ” በሚል በዓመቱ የተከናወኑ አንኳር ጉዳዮችን፣ የተገኙ ውጤቶችና ለቀጣይ ሥራዎች የተወሰዱ ትምህርቶች አስመልክቶ የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት አመራሮች በተገኙበት ገለጻ አድርጓል።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሀብታሙ ሲሳይ ባደረጉት ገለጻ፤ በየደረጃው የኮሚሽን አደረጃጀት ለማጠናከር መሰራቱን፣ የአሰራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት በኮሚሽኑ ጸድቀው ተግባራዊ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።

በየደረጃው የሚገኘው የኮሚሽን አመራርና አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠቱን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም በመሻሻል ዲጂታል ብልፅግናን የመፍጠር ሂደት መከተሉን፣ የኢንስፔክሽንና የቁጥጥር አቅም ማደጉን እንዲሁም አዲስ የስራ ባህል ለመፍጠር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የእቅድ አፈጻጸም ወጥነት እንዲኖረው ጠንካራ ኢንስፔክሽን ለጠንካራ ፓርቲ የሚል መሪ ሀሳብ ተግባራዊ መደረጉ ወጥ የአሰራር ስርዓት እንዲኖር ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ከቅንርጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በቅርብ የክትትል፣ የድጋፍና የግምገማ ስርዓት በመዘርጋቱ የአፈጻጸም መቀራረብንና በኮሚሽኑ አመራሮችና አባላት መካከል ቤተሰባዊ ቅርርብን መፍጠር ስለመቻሉ በገለጻቸው ጠቅሰዋል።

የኮሚሽኑ አደረጃጀት በየጊዜው ኢንስፔክሽን በማካሄድ ለሚመለከታቸው የፓርቲ መዋቅሮች ግኝቶችን ከምክረ ሃሳብ ጋር በመስጠት ለጠንካራ ፓርቲ ግንባታ የበኩሉን ሚና እንደተጫወተ ተገልጿል።

ይህም በፓርቲ አባላትና አመራር ዘንድ ተደማጭነቱና ተዓማንነቱ እየጨመረ መምጣቱን መናገራቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.