የሀገር በቀል እውቀቶች በምርምር ሊደገፉ እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል እውቀቶችን ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ለመጠቀም በምርምርና በቴክኖሎጂ ሊደገፉ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ያሉ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች ላይ ሲያካሂድ የቆየውን የዳሰሳ ጥናትና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፖርታል ሰርቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡
ምክክሩ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የሀገር በቀል እውቀቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በማዘመን የኢኮኖሚው እድገት ማሳለጫ አንድ ምዕራፍ አድርጎ ለመጠቀም ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በምክክሩ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)÷የሀገር በቀል ዕውቀቶችን በምርምር በመደገፍ ከውጪ የሚመጡትን በማስቀረት እራሳችንን ችለን ለሌሎች ለመትረፍ በሚያስችል ስነ ምህዳር ላይ በመደራጀትና በመተባበር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር መሪ ስራ አስፈፃሚ ተክለማሪያም ተሰማ (ዶ/ር በበኩላቸው÷የምርምር ድጋፍ የሚፈልጉ የሀገር በቀል እውቀቶች መረጃዎችን በማዘመን በሁሉም የአለም ሀገራት እውቅና እንዲያገኙና ወደ ሀብት ተቀይረው ተጠቃሚነታቸው እንዲሰፋ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሀገር በቀል እውቀቶች ናቸው ተብለው በምርምር የተረጋገጡና እውቅና ያገኙትን በፖርታል በማስቀመጥ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ይደረጋል ማለታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡