ወደ ሰላም የተመለሱ ታጣቂዎችን አርአያነት ሌሎች የታጠቁ ሃይሎችም እንዲከተሉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የኦነግ ታጣቂዎች ከፍተኛ አመራር አባላት መካከል በተደረገው የሰላም ስምምነት መሰረት የተመለሱ ታጣቂዎችን አርአያነት በመከተል የቀሩትም እንዲመጡ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ጥሪ አቀረበ።
የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ በሰጠው መግለጫ የህብረቱ ሰብሳቢና የመጫ ኦሮሞ አባ ገዳ ወርቅነህ ተሬሳ ÷ በጫካ የቀሩ ታጣቂዎች የቀረበውን “የሰላም አማራጭ በመከተል እንዲገቡ እንፈልጋለን” ብለዋል።
በክልሉና በሀገር አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውንም ገልፀው በጫካ ያሉ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ሰምተው እንዲመለሱ ዳግም ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት።
ሃደ ሲንቄዎች፣ ወጣቶችና ምሁራንን ጨምሮ ሌሎችም ሰላምን በመስበክ “በክልሉ የተገኘውን ሰላምና ዕርቅ ለማፅናት ተባብረን መስራት ይገባናል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለሰላምና ለአንድነት ዘብ መቆም አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።