Fana: At a Speed of Life!

የጸጥታ ችግር በሰሊጥ ምርት አቅርቦት ላይ ፈተና ሆኗል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተያዘው የበጀት ዓመት 1 ሚሊየን 800 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ያቀደው የአማራ ክልል 771 ሺህ 360 ኩንታል ሰሊጥ ለገበያ ማቅረብ መቻሉን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር የሰሊጥ ምርትን ወደ ገበያ በሚፈለገው ልክ ለማቅረብ እንዳላስቻለ ተገልጿል።

በተያዘው የበጀት ዓመት 1 ሚሊየን 800 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ለገበያ ለማቅረብ ዐቅደው ወደ ሥራ መግባታቸውን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አትክልት አሳቤ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

እስከ ትናንት ምሽት ድረስም 771 ሺህ 360 ኩንታል ሰሊጥ ለገበያ ማቅረብ መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሰሊጥ ምርትን ከአርሶ አደሩ ማሳ ጀምሮ ለገበያ ለማቅረብ በሚደረጉ ሂደቶች የጸጥታ ችግር መጉላላት በመፍጠር እንደፈተናቸው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ዘረፋን ጨምሮ የመንገድ መዘጋጋት እንዲሁም በየኬላዎች ሰሊጡን በታሰበው ጊዜ እንዳይጓጓዝ መሠናክሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ቢሮው ችግሮችን በመቋቋም በሥራ ሠዓት ብቻ ሳይገደብ በተቻለ መጠን ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ርብርብ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሰሊጥ ምርቱ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ጥቅም እንዲያበረክት ከክልሉ የጸጥታ አካላት እስከ መከላከያ ሠራዊት የሚደርስ እጀባ እንደሁኔታው እንዲሰጥ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የሰሊጥ ምርት የሀገር እና ሕዝብ ሀብት ነው ያሉት ወ/ሮ አትክልት÷ ይህ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ውሎ የሚጠበቅበትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲያስገኝ ሁሉም ለሰላም መስፈን ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጸጥታውን በማወክ ምርት ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት የሚያስተጓጉሉ አካላትን ለመከላከል ሕብረተሰቡ የሚያደርገውን ትብብር ይበልጥ እንዲያጠናክርም ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.