የኢጋድ የህጻናት ረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ የቴክኒክ ሙያተኞች ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የህጻናት ረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ የቴክኒክ ሙያተኞች ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀመረ።
ፖሊሲው በኢጋድ ቀጣና የሚኖሩ ህጻናት የሚያጋጥማቸውን ችግር በመፍታት ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የአሰራር ማዕቀፎችን የሚዘረጋ ነው።
በተመሳሳይ አባል ሀገራቱ ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር በህጻናት መብት ላይ ለመስራት ያስችላል ተብሏል።
ፖሊሲው በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን፣ መገለል፣ የጉልበት ብዝበዛና ሌሎች በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ የሚደረጉ እቅዶችን አስቀምጧል።
ቀደም ሲል በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በአባል ሀገራቱ ከሚመለከታቸው አካላት፣ ህጻናት ፓርላማና ከሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ግብዓት መሰብሰቡ ተመላክቷል።
የቴክኒክ ሙያተኞች ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚያደርጉት ውይይት ለረቂቅ ፖሊሲው በግብዓትነት የሚያግዙ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ሲሆን÷ ታህሳስ 4 ቀን 2017 በሚካሄደው የኢጋድ ሚኒስትሮች ስብሰባ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
እየተካሄደ ባለው ኮንፈረንስ ከአባል ሀገራቱ የተወከሉ የዘርፉ ከፍተኛ ሙያተኞች፣ የህጻናት ፓርላማ ተወካዮች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡